ወደ ክልላችን የሚመጣ ባለሥልጣንም ሆነ እንግዳ ያለ አጃቢ በነፃነት የሚንቀሳቀስበት ሁኔታ ተፈጥሯል

የሶማሌ ክልል በፀጥታና ሰላም እንዲሁም በማህበራዊ ልማት አበረታች ውጤቶችን አስመዝግቧል።

የክልሉ ፕሬዚዳንት በ2007 ለአዲስ ዘመን በሰጡት ገለጻ በርካታ ክንውኖችን ያተቱ ሲሆን፤ ከነዚህ መሀከል የጸጥታ መሻሻል፣ የመጠጥ ውሃ ተደራሽ እና የህክምና አቅርቦት ይገኙበታል።

የክልሉ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር አብዲ መሐመድ ኡመር እንዳስታወቁት፤ የፀረ ሰላም ኃይሎች በሚያደርጉት እንቅስቃሴ የክልሉ ሕዝብ ለፀጥታ ስጋት ተጋልጦ ቆይቷል፡፡ ይህም በክልሉ አመርቂ የሚባል ልማት ማስመዝገብ አዳጋች አድርጎት ነበር፡፡ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ግን የክልሉ መንግሥት በሰጠው ልዩ ትኩረትና ከፌዴራል መንግሥት ባገኘው ድጋፍ የፀረ ሰላም ኃይሎቹን በማስወገድ አስተማማኝ የሚባል ሰላም ማስፈን ተችሏል፡፡

«አሁን አሁን ማንኛውም ወደ ክልላችን የሚመጣ ባለሥልጣንም ሆነ እንግዳ ያለ አጃቢ በነፃነት የሚንቀሳቀስበት ሁኔታ ተፈጥሯል» ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ለእዚህም ውጤት መመዝገብ የሕዝቡ ሚና ከፍተኛ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ በየደረጃው አመለካከትን የመቀየር ሥራም በመሰራቱ ፀረ ሰላም ኃይሎችን ትጥቅ በማስፈታት ወደ ሰላም እንዲመጡና የልማቱ አጋር ማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡

በሌላ በኩልም በእቅድ ዘመኑ ከተሰሩት የልማት ሥራዎች መካከል የክልሉን ሕዝብ የመጠጥ ውሃ ተደራሽነት ለማሳደግ የተሰራው ሥራ አበረታች የሚባል መሆኑን አቶ አብዲ አመልክተዋል፡፡

እንደ እርሳቸው ገለፃ ከክልሉ ሕዝብ 85 በመቶ አርብቶ አደር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በውሃ እጦት ይሰቃይ ነበር፡፡ በተለይም እናቶችና ሕፃናት ውሃ ፍለጋ በሚያደርጉት ረጅም ጉዞ ምክንያት እስከ ሞት የሚደርስ ጉዳት ያጋጥማቸዋል፡፡የክልሉ መንግሥት በተለይም ባለፉት አምስት ዓመታት የሕዝቡን የመጠጥ ውሃ ችግር በመሠረታዊነት መፍታት የሚያስችሉትን መርሐ ግብሮች ነድፎ ተንቀሳቅሷል፡፡

ከእነዚህም መርሐ ግብሮች መካከልም የተፈጥሮ የውሃ አካላቶችን ወደ ልማት የማስገባቱ ሥራ ትልቅ ትኩረት የተሰጠው እንደነበር ጠቅሰው፤ በዚህም በሺዎች የሚቆጠሩ የክልሉ ሕዝቦች ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውን ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም ከ480 በላይ የውሃ ጉድጓዶች መቆፈር መቻሉን ተናግረው፤ በተለይም 550 ሜትር ጥልቀት ያለውና እስከ አንድ ሺ ኪዩቢክ ሜትር ውሃ መያዝ የሚችለው የውሃ ጉድጓድ በአገር አቀፍ ደረጃ ቀዳሚ የሚያደርገው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ከጤና ተቋም አኳያም «ከዚህ ቀደም በክልላችን ደረጃ የነበሩትን አራት ሆስፒታሎች ወደ ዘጠኝ አድርሰናል፤ አንድ ተጨማሪ ሪፈራል ሆስፒታልም ገንብተናል» ብለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የጤና ተቋማት ከዘጠኝ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ እየተገለገለ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ከዚህ ቀደም በወሊድ ምክንያት ይሞቱ የነበሩ እናቶችና ሕፃናትን ሕይወት ማትረፍ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

እንደ አቶ አብዲ ገለፃ በእቅድ ዘመኑ በአጠቃላይ የተሰሩት የልማት ሥራዎች አበረታች ተብለው የሚወሰዱ ቢሆንም በተለይም አርብቶ አደሩን ወደ ከፊል አርብቶ አደር የማምጣቱ ሂደት ብዙ ሊሰራበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ለእዚህም የሕዝቡን አመለካከት መለወጥና ግንባር ቀደም ተሳታፊ ማድረግ ይጠይቃል፡፡

************

ምንጭ:- አዲስ ዘመን – July 2015