የኢትዩጲያ ሶማሌ ክልል ለተፈናቃዩች መመለስ ዋስትና የሆኑ ነጥቦች

የኢትዩጲያ ሶማሌ ብሄራዊ ክልል ላለፉት ሁለት ወራት ከክልሉ ዋና ከተማ ጅግጅጋ እና ወቻሌ አካባቢዎች የተፈናቀሉ የኦሮሞ ተወላጆችን ወደ ቀዬያቸው ሲመልስ ነበር፡፡ የክልሉ ርእሰ መስተዳደር አቶ አብዲ መሀመድ ኡመር ባሳለፍነው ሳምንት ለዛሚ ብቻ በሰጡት ቃለምልልስ አሁንም ያልተመለሱ ተፈናቃዩች እንዲመለሱ ሲጠይቁ ክልሉ ለደህንነታቸው ሀላፊነት እንደሚወስድ ተናግረው ነበር፡፡

ቅዳሜ ታህሳስ 15 ቀን ርእሰ መስተዳደሩ በጽህፈት ቤታቸው ለጋዜጠኞች ወቅታዊ ጉዳዩችን በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ በወቅቱ ዛሚ ተፈናቃዩች እንዲመለሱ ጥሪ ስታቀርቡ የምትሰጡት ዋስትና ምንድነው ብሎ ጠይቋል፡፡

ርእሰ መስተዳደሩ በመጀመሪያ በወቅቱ የነበረው የፖለቲካ አለመረጋጋት አሁን ሙሉ ለሙሉ መቆሙን አስታውቀዋል፡፡ በኦሮሚያ እና የኢትዩጲያ ሶማሌ ክልሎች ወሰን ላይ የሁለቱም ክልሎች የጥበቃ ሀይሎች እንዲነሱ ተደርጓል፡፡ በምትኩም የኢትዩጲያ መከላከያ ሰራዊት ወታደሮች በተደጋጋሚ ግጭት የታየበት ወሰን ላይ ጥበቃ እያደረጉ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሁለቱም ክልሎች የጥበቃ ሀይሎችን ከድንበራቸው አምስት ኪሎ ሜትር ለማራቅ ተስማምተዋል፡፡ ይህን ስምምነት ተላልፎ የሚገኝ የየትኛውም ክልል የጥበቃ ሀይል በሀገሪቱ ህግ መሰረት ተጠያቂ ይደረጋል፡፡

የኢትዩጲያ ሶማሌ ብሄራዊ ክልል እና የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልል ከመኤሶ እስከ ሞያሌ ከ2ሺህ ኪሎሜትር በላይ የድንበር መስመር ይጋራሉ፡፡

በሁለተኛነት ከኢትዩጲያ ሶማሌ የተፈናቀሉ የኦሮሚያ ክልል ተወላጆች እንዲመለሱ ሀላፊነት መውሰዳችንን ያሳያል ሲሉ አቶ አብዲ መሀመድ ያስቀመጡት ነጥብ ሁለቱም ክልሎች ከሚያከብሯቸው እና ከሚቀበሏቸው የሀገር ሽማግሌዎች ጋር አብረው እየሰሩ መሆናቸውን እና ወደ ቀዬያቸው የሚመለሱትን ዜጎች በማንኛውም መንገድ ከኢትዩጲያዊነታቸው ውጪ ጽንፈኛ በሆነ መንገድ ለሚያያቸው ሰው ውግዘት እንደሚደርስበከት እና በአካባቢው ስርአት መሰረትም እንደሚጠየቅ ተናግረዋል፡፡

የእነዚህ ሁለት ክልሎች የድንበር አካባቢ ነዋሪዎች ለዘመናት በተደጋጋሚ ግጭቶች ይከሰትባቸው የነበሩ ቦታዎች ናቸው፡፡ በተለያዩ ወቅቶች የታየውም ነዋሪዎቹ እንዲጋጩ ምክንያት የነበረው ደግሞ በአካባቢው የነበረው ተፈጥሮአዊ ሀብት እና የዜጎች ፍላጎት አለመመጣጠን ነበር፡፡ ነገር ግን ከ2008 አ.ም በፊት በአካባቢዎቹየ ተከሰቱት ግጭቶች ከሀገር ሽማግሌዎች እርቅ ይፈታ ነበር፡፡ አሁን ተፈናቃዩችን ለመመለስም ወደ ቀደመው መንገድ እንደሚመለሱ ተናግረዋል፡፡

ነገር ግን ይህን ለማሳካት እንዳይቻል እና ግጭቶቹ በተደጋጋሚ እንዲከሰቱ ምክንያት ያሏቸውን ተግዳሮቶችንም አስቀምጠዋል፡፡

እንደ አቶ አብዲ ገለጻ አሁን እየተፈጠሩ ያሉት ግጭቶች ለየት ያሉ ናቸው፡፡ኢትዩጲያ ባለፉት ጥቂት አመታት የታላቁ ህዳሴ ግድብን እና ክልሎችን የሚያስተሳስሩ የመንገድ እና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን ጀምራለች፡፡ አቶ አብዲ እነዚህ ፕሮጀክቶች የሀገር ውስጥም የውጪም ጠላት አላቸው ብለዋል፡፡ እነዚህ ጠላቶች ፕሮጀክቶችን የሚያስቆሙበት መንገድ ይፈልጋሉ፤ማንን ከማንማጋጨት እንዳለባቸው ይማከራሉ፡፡ ነዋሪዎች ደግሞ ባለማወቅ የእነዚህ ጠላት ሀይሎች መጠቀሚያ ይሆናሉ ብለዋል፡፡

ባለፉት ወራት ከኢትዩጲያ ሶማሌ እናከ ኦሮሚያ ብሄራዊ ክልሎች ባሻገር በአንዳንድ የሀገሪቱ ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ የጉዳት መጠናቸው የተለያዩ ወደ ግጭት ያመሩ አለመግባባቶች መከሰታቸው ይታወሳል፡፡

አሁን የኢትዩጲያ ሶማሌ ብሄራዊ ክልል ርእሰ መስተዳደር አቶ አብዲ ከክልሉ ሁለት ቦታዎች የተፈናቀሉትን ዜጎች ወደ ቀዬያቸው እንዲመለሱ ጥሪ ሲያቀርቡ በሶስተኛ ደረጃ በዋስትናነት ያቀረቡት የሁለቱ ክልሎች ነዋሪዎች የአንዱ ተወላጅ በሌላው ሲኖር ከባህል እና ሀይማኖት መመሳሰል እና ቢለያዩም እንኳን ተከባብሮ በጋራ ከመኖር ባሻገር በጋብቻ የተሳሰሩ ብዙ ቤተሰቦች መኖራቸውን ነው፡፡

በኢትዩጲያ ሶማሌ ክልል የመንግስት መስሪያ ቤቶች የክልሉ ልዩ የፖሊስ ሀይልን ጨምሮ በተለያየ የስራ ደረጃ ላይ የሚገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ የኦሮሞ ተወላጅ ኢትዩጲያውያን ይገኛሉ፡፡

እንደ ርእሰ መስተዳደሩ መግለጫ ደግሞ ከክልሉ ቁልፍ ፕሮጀክቶች መካከል በኦሮሞ ተወላጅ ኢትዩጲያውያን ኢንጂነሮች የሚመሩት ፕሮጀክቶች በጣት ከሚቆጠረው በላይ ናቸው፡፡

አቶ አብዲ መሀመድ ተፈናቃዩችን ለደህንነታቸው ዋስትና ሰጥቶ መመለስን በተመለከተ የተናገሩት የመጨረሻ አስተያየታቸው የሚከተለው ነበር፡፡

‹‹እኛ የሚቆጨን መጀመሪያ የኦሮሞ ተወላጆች ተፈናቅለው ሲወጡ ካራማራ ላይ ቆመን በቀዬያቸው እንዲቆዩ አለመለመናችን ነው፡፡››

*********

ምንጭ:- ዛሚ ራዲዮ