ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ለፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ምላሽ ምስጋና አቀረቡ

አዲስ አበባ ( kalitimes)ሰኔ 13/2010.የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዶክተር አብይ አህመድ የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ለኢትዮጵያ መንግስት የእርቅና ድርድር ጥሪ ለሰጡት ምላሽ ምስጋና አቀረቡ።

በመልዕክታቸውም ኢትዮጵያ የኤርትራን የልዑካን ቡድንን በታላቅ አክብሮት ተቀብላ ለማስተናገድ ዝግጁ መሆኗን ነው ያስታወቁት።

የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ምላሻቸውን የሰጡት በየዓመቱ በሚከበረው የሰማዕታት መታሰቢያ ቀን ላይ በቀጥታ ቴሌቪዥን ስርጭት ባደረጉት ንግግር ሲሆን፥ በድንበር ጉዳይ ላይ የሚነጋገር የሃገራቸውን ልዑክ ወደ አዲስ አበባ ለመላክ ማሰባቸውን ነው ዛሬ ጧት ላይ የተናገሩት።

በአፍሪካ ቀንድ በተለይም በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታዩ ያሉት ለውጦች ተገቢ ትኩረት የሚፈልጉ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት በሽግግር ላይ ትገኛለች ያሉት ፕሬዚዳንቱ፥ አሁን ላይ የቀረው በሁለቱ ሀገራት መካከል የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ወደ ነበረበት ለመመለስ ቅድሚያ ተሰጥቶት ይሰራል ነው ያሉት።

ለዚህም በዜና ከመከታተል እና ከመቀባበል በዘለለ ያለውን ሁኔታ በቀጥታ ማወቅ ስለሚያስፈልግ፤ እንዲሁም በቀጣይ ሊሰራበት ስለሚገባ የልዑክ ቡድን ወደ አዲስ አበባ እንደሚላክ አስታውቀዋል፡፡

በተያያዘ ዜናም ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ባላት ግንኙነት አዲስ ምዕራፍ መጀመር እንደምትፈልግ የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ከኤርትራ ጋር ያለውን የድንበር ችግር በሰላም ለመፍታት የአልጀርሱን ስምምነት እና የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጁነቱን መግለጹ ይታወሳል።

የኤርትራ መንግስትም ይህንን የሰላም ሃሳብ እንዲደግፍ መንግስት የሰላም ጥሪ ማቅረቡም የሚታወስ ነው።

የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂም በዛሬው እለት በኤርትራ የቴሌቪዥን ጣቢያ ባደረጉት ንግግር፥ የድንበር ችግሩን ለመፍታት ወደ አዲስ አበባ የልዑካን ቡድን ለመላክ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

አዲስ አበባ የሚመጣው የልዑካን ቡድን በድንበር ችግሩ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር በመነጋገር በቀጣይ ሁኔታዎች ላይ የሚመክር ይሆናልም ተብሏል።

የኢትዮጵያ መንግስትም ይህን የኤርትራ ምላሽ በበጎ መልኩ የተቀበለ ሲሆን፥ በሁለቱ ሃገራት መካከል ለሚደረገው ንግግር ዝግጁ መሆኗን በድጋሚ እንደምታረጋግጥ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል።

ኢትዮጵያ ዕርምጃው በሁለቱ ሃገራት መካከል ያለውን ግንኙነት በማሻሻል ለቀጠናው መረጋጋትና ልማት ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል ብላ እንደምታምንም ነው ሚኒስቴሩ የገለጸው።

በመሆኑም ከድንበር በላይ የሆነውን የሁለቱ ሃገራት ህዝቦች ግንኙነት ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር ኢትዮጵያ ቁርጠኛ መሆኗንም ባወጣው መግለጫ ጠቅሷል።

%d bloggers like this: