ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ ግጭት ለመቀስቀስ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን የታዳጊ ክልል ወጣቶች በንቃት እንዲጠብቅ ጥሪ አቀረቡ

አዲስ አበባ (kalitimes)ሰኔ 25 ፣ 2010. የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በታዳጊ ክልሎች ግጭት ለመቀስቀስና ሰላምን ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን ህብረተሰቡ በንቃት እንዲጠብቅ ጥሪ አቀረቡ።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በታዳጊ ክልሎች የእርስ በእርስ ግጭት ለመቀስቀስ እየተሰሩ ያሉ ሴራዎችን ህብረተሰቡ ነቅቶ መጠበቅ እንደሚገባው ዛሬ በሰጡት ወቅታዊ መግለጫ ተናግረዋል።

በታዳጊ ክልሎች አዳዲሰ ኃይሎችና ፀጉረ ልውጥ ሰዎች እየተንቀሳቀሱ የሚያደራጁት ኃይል ካለ ስርዓቱ ብቻ ሳይሆን ወጣቶች ነቅተው እንዲጠብቁም ጥሪ አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች ሰላም ለመመለስ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ተጨባጭ ስራ ለሰሩት ወገኖችም ምስጋና አቅርበዋል።

ከ15 ቀን በፊት በደቡብ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ከአካባቢው ህብረተሰብ ጋር ባደረጉት ውይይት እና ባስቀመጡት አቅጣጫ መሰረት፥ የየአካባቢው የህብረተሰብ ክፍሎች ለሰጡት ፈጣን ምላሽ ምስጋናቸውን አድርሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በመንግስት በኩል የተጀመሩ የለውጥ እንቅስቃሴዎችን በመደገፍ በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች እየተደረጉ ላሉ የድጋፍ ሰልፎችም ምስጋና አቅርበዋል።

በቀጣይም ህብረተሰቡ የድጋፍ ሰልፉን ገታ በማድረግና ኃይሉን በመጠቀም ወደ ልማት ሥራዎች እንዲሰማራም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ከአሁን በኋላ ሰልፉን በመቀነስና በመሰባሰብ ችግኝ በመትከል፣ አካባቢን በማዕዳት፣ ትምህርት ቤቶች አካባቢ የፈራረሱ ቦታዎችን በመጠገን፥ ጉልበትን በልማትና በስራ ማዋል ይገባል ብለዋል።

የዘንድሮው የክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባልም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው።

ዶክተር አብይ በቀጣይ ሁለት ወራት የሚካሄደውን የክረምት ወራት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ግብ ሰፋ በማድረግ ወጣቶች በመኖሪያ አካባቢያቸው ብቻ ሳይወሰኑ ኢትዮጵያዊነትን የሚያጎላ ተግባር ሊፈፅሙበት ይገባልም ነው ያሉት።

መረጃውን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አድርሶናል።

 

%d bloggers like this: