ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት የገመል ስጦታ ተበርክቶላቸዋል

ሃዋሳ(kalitimes.com)ሐምሌ 7/2010ዓ.ም በዛሬው እለት በኢትዮጵያ መንግሥት ጋባዥነት ይፋዊ ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙት የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ህዝብ እና መንግሥት በኢፌዴሪ ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በኩል የግመል ስጦታ ተበርክቶላቸዋል። ግመል በሁሉም የኢትዮጵያ አርብቶ አደር ማህበረሠብ በተለይ በኢትዮጵያ ሶማሌ እና በአፋር ክልሎች ህዝብ የጥንካሬ፣ የሃብት እና የአብሮነት ተምሳሌት ከመሆኑም ባሻገር በተለይም በኤርትራ ህዝብ የነፃነት ትግል ወቅት ታጋዮቹ ከቦታ ቦታ በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ትጥቅ እና ስንቅ እንዲሆናቸው ይጠቀሙት ነበር። ግመል ለኤርትራዊያን ከዚህም ያለፈ ትርጉም ያለው መሆኑም ተገልጿል።

በተያያዘም ግመል የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል መንግሥት ባንዲራ አርማ ከመሆኑም በተጨማሪ የክልሉ መሪ ድርጅት ኢሶህዴፓ ዋና መለያ በመሆንም ይታወቃል። ከዚህ ጋር ግመል የኤርትራ መንግሥትና የሃገሪቱ መሪ ድርጅት ብሔራዊ አርማ ሲሆን፤ በዚህ አሁን በተፈጠረው የሁለቱ ሃገር ህዝቦችን ቅርርብ እና ትስስር የሚያጠናክር መሆኑንም ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ገልፀዋል። በዛሬው እለት በሃዋሳ ከተማ ይፋዊ ጉብኝት ላይ ለሚገኙት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ለክብራቸው በተዘጋጀው የእራት ግብዣ ላይ ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ህዝብ እና መንግሥት የተበረከተላቸው የግመል ስጦታን በደስታ በመቀበል ለኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ አብዲ መሀሙድ ዑመር የላቀ ምሥጋናቸውን አቅርበዋል።

more recommended stories