የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ም/ቤት የክልሉን የ2011 ዓ.ም በጀት 16,871,585,843 ብር አደርጎ አፅድቋል

ጅግጅጋ(kalitimes)ሐምሌ 08/2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ም/ቤት ለሶስት ተከታታይ ቀናት ባደረገው 7ተኛው መደበኛ ጉባኤ የ2011 ዓ.ም በጀትን ማፅደቁ ተገለፀ። የ2011 ዓ.ም በጀት በዋናነት በወጣቶች የሥራ ፈጠራ፤የቤቶች ልማት እና በሌሎች የመሠረተ ልማት አውታሮች ላይ እንዲውል መወሰኑንም ም/ቤቱ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ም/ቤት የ3 ቀናት ጉባኤ በማድረግ በትላንት እለት የክልሉን የ2011 ዓ.ም በጀት 16,871,585,843 (16 ቢሊዮን 871 ሚሊዮን 585 ሺህ 843)ብር አድርጎ ማፅደቁን  የክልሉ ም/ቤት አፈ ጉባኤ  አቶ መሀመድረሺድ ኢሳቅ አስታውቋል።በዚህም ክልሉ በ2010 የበጀት ዓመት ከነበረው ጋር ሲነፃፀር የ1.6 ቢሊዮን ብር ጭማሪ እንዳሳየም ም/ቤቱ አብራርተዋል።

ከአጠቃላይ በጀቱ ውስጥም 3 ቢሊዮን የሚሆነውን ከክልሉ ገቢ ለመሰብሰብ የታለመ ስለመሆኑ የቀድሞው የፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አህመድ አብዲ አስረድቷል።በ2011 ዓ.ም የክልሉ በጀት በዋናነት በወጣቶች ሥራ ዕድል ፈጠራ እና በቤቶች ልማት ላይ እንደሚውልም ሃላፊው ገልጿል። በተለይ የመንግሥት ሠራተኞችና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የማህበረሠብ ክፍሎችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ በተለያዩ የክልሉ ከተሞች የቤት ልማት ፕሮጀክቶች እንደሚከናወኑና በክልሉ መንግሥት መ/ቤቶች ባሉት ክፍት የሥራ መደቦች ላይም ሙሉ በሙሉ በተማረ የሰው ሃይል እንደሚቀጠርምም መወሰኑ ታውቋል። ከዚህ በዘለለም ደግሞ ለወጣቶች እና ሴቶች ብድር በመመቻቸት የሥራ ዕድል ፈጠራ እንደሚከወን የቀድሞው ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊና የውሃ ልማት ቢሮ ሃለፊ አቶ አህመድ አብዲ አስታውቋል።

በሌላ በኩል በክረምት ወቅት እንደ ዋቢ ሸበሌ ያሉት ወንዞች በሚሞሉበት ጊዜ በተፋሰሱ ዙሪያ የሚኖሩ የህብረተሠብ ክፍሎች ላይ የሚደርሱት ጉዳቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ይገኛል። የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልልም በየዓመቱ ይሄንን ጉዳይ ትኩረት እየሰጠውና በጀት እያስቀመጠለት እና እየበጀተለት በዙሪያው የሚኖሩ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ሥራዎች ሲሠሩ መቆየታቸውን ም/ቤቱ ገልጿል።

ታዲያ በ2011 የበጀት ዓመትም በተፋሰሱ ዙሪያ የሚኖሩትን ዜጎች የአደጋ ተጋላጭነት ለመቀነስ እንዲሁ የታሰበ ሲሆን በዚህ ላይም ከክልሉ በጀት በተጨማሪ የፌዴራል መንግሥት እገዛም እንደሚኖር አቶ አህመድ አብዲ ገልጿል። በጀቱ ለተያዘለት አላማ እንደሚውልም ከዚህ ቀደም ይሠራበት እንደነበረው የፋይናንስ ሥርዓትን በጠበቀ መልኩ የክትትልና ድጋፍ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ሃለፊው አክለው ገልፀዋል።

more recommended stories