የኢ.ሶ.ክ ሃገር ግማግሌዎች በሃገር ውስጥና በውጭ ሃገራት ለሚገኙ የክልሉ ተወላጆች በሙሉ በጅግጅጋ ከተማ በሚካሄደው የሰላም ኮንፈረንስ ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ አቀረቡ

 

ጅግጅጋ(kalitimes)ሐምሌ 16/2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ሃገር ሽማግሌዎች፣ ገራዶች፣ ኡጋሶች፣ ሱልጣኖች፣ ወበሮችና ሌሎችም በመላው የክልሉ ህዝብ ዘንድ ክብርና ተቀባይነት ያላቸው የጎሳ መሪዎች በዛሬው እለት በጅግጅጋ ከተማ በራሳቸው ተነሳሽነት በጋራ ባወጡት የአቋም መግለጫ በሃገር ውስጥና በውጭ ሃገራት ለሚገኙ የክልሉ ምሁራን፣ ደጋፊዎች፣ በፖለቲካ ተፎካካሪ ግለሰቦች፣ የፖለቲካ ተፎካካሪ ድርጅቶች፣ አመራሮች፣ ወጣቶች፣ ሴቶችና ሌሎችም የክልሉ ማህበረሰብ ክፍሎች እንዲሁም መላው የክልሉ ተወላጆች በአጠቃላይ ሐምሌ 28 ቀን፤2010ዓ.ም ወይንም እ.ኤ.አ ኦውገስት 5/2018 በጅግጅጋ ከተማ በሚካሄደው የሰላምና አንድነት ኮንፈረንስ ላይ እንዲሳተፉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

በኮንፈረንሱ ላይም በክልሉ የጋራ መግባባት ምክክር አልፎ አልፎ የሚታዩ ልዩነቶችን የሚቀረፉበትና ወደ ተሻለ አንድነትና የጋራ መግባባት የሚሸጋገሩበት የህዝብ ኮንፈረንስ ሲሆን፤ በዚህም በዋናነት የክልሉን ሰላም፣ ልማትና አንድነት አጠናክሮ በመጓዝ ሂደቶች ዙሪያ የሚወያዩበት ታላቅ ጉባኤ እንደሆነም የሃገር ሽማግሌዎቹ ገልጸዋል። በተጨማሪም በሰላም ኮንፈረንሱ ላይ የክልሉ ምሁራን፣ የክልሉ መሪ ድርጅት ደጋፊዎች፣ ተፎካካሪ ግለሰቦች፣ የፖለቲካ ተፎካካሪ ድርጅቶችና አመራሮች፣ ወጣቶች እንዲሁም ሌሎች በክልሉ ህብረተሰብ ዘንድ ተሰሚነትና ተቀባይነት ያላቸው ግለሰቦችም እንደሚሳተፉ የሃገር ሽማግሌዎቹ ቃል አቀባይ የሆኑት ገራድ ኩልሚዬ ጋራድ መሀሙድ አሳውቀዋል።

በመጨረሻም በቅርቡ ከአሸባሪነት ዝርዝር ውስጥ ስማቸው ከተሰረዙት መካከልም የኦብነግ(የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጪ ግንባር)አባላት በሰላምና አንድነት ኮንፈረንሱ ላይ እንዲገኙና ልክ እንደሌሎቹ የሃገሪቱ የፖለቲካ ተፎካካሪ ድርጅቶች ሁሉ እነሱም በክልላቸውና በሃገሪቱ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሂደቶች ላይ እንዲወያዩ ጥሪው የሚያካትታቸው ሲሆኑ፤ በተጨማሪም በሃገሪቱ እየተደረገ ባለው ይቅር መባባል፣ መከባበርና ሃገራዊ አንድነት እነሱም እንዲደመሩ የሃገር ሽማግሌዎቹ ተወካይ ገራድ ኩልሚዬ ጋራድ መሀሙድ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

source:-cakaaranews.com