የኢንጂነሩ ሞት ምን ይነግረናል?


በኃይሉ ሚዴቅሳ ፍስሐጽዮን. በ1960ዎቹ መጨረሻ የከተማ ግድያ የተጀመረው ሥም ያላቸውን ሰዎች በአደባባይ በመረሸን ነበር፡፡ ዶ/ር ፍቅሬ መርዕድ ሚስቱን እየጠበቀ መኪና ውስጥ ተገደለ፡፡ በዚያች ተኩስ የተጀመረው የከተማ አናርኪዝም ዘመን የማይሽረውን የቀይሽብር ታሪክ ትቶልን አለፈ፡፡በወቅቱ ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ሁለቱን ወገን እያጋደለ እሳቱን መሞቅ ነበር የያዘው፡፡ አንዱን እያስታጠቀ ሌላውን አስፈጀ፡፡ፍትህ በተኳሽ ላይ ወደቀች፡፡ገዳይ ለፍርድ ሳይቀርብ ሌላ ግድያ እያስከተለ ቀጠለ፡፡

አሁንም እንዲያ ወዳለ ዘመን ላይ እየሄድን ላለመሆኑ ዋስትና የለንም፡፡መንግሥትም በይቅርታ ሰበብ አገሩን በሙሉ ‹የእንተወው›› ፖለቲካ ላይ ጥሎታል፡፡ የተለያየ ቁርሾ፣ፀብ፣ቅሬታ፣ባለበት ማኅበረሰብ፣ባልነቃና ምክንያታዊ መሆን በተሳነው ማኅበረሰብ፣ ብዙ ታሪካዊ ጠላቶች ባሉበት ሀገር ላይ ነገሮችን በይቅርታ ስም አድበስብሶ ማለፍ አመክንዮ የለውም፡፡

የዳንጎቴ ስሚንቶ ፋብሪካ ስራ አስኪያጅ፣ ጸሃፊና ሾፌር የተገደሉበት ዝርዝር ሁኔታና የገዳዮቹ ማንነት፣ለግድያ ያበቃቸው ሰበብና ከጀርባ ያለው ዝርዝር ታሪክ፣እነሱም ላይ ምን እርምጃ እንደተወሰደባቸው፣ስለመያዛቸውም ጭምር፣ ሒደቱ ምን ላይ እንዳለ አይታወቅም፡፡

መስቀል አደባባይ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለመደገፍ ተብሎ በተጠራ ሰልፍ ላይ ፈንጅ ያፈነዱ ሰዎች እነማን እንደሆኑ እና ምን ህጋዊ እርምጃ እንደተወሰዳባቸው ለሕዝብ የተነገረ ነገር የለም፡፡

በደቡብ ክልል ላይ ያ ሁሉ እልቂት እንዲካሄድ የሆነው እንዴት እንደሆነ “የቀን ጅቦች“ ከሚል ማስፈራሪያና ፍረጃ ውጭ የተነገረ መረጃ የለም። ‹‹የቀን ጅብስ ማነው፣ ለምንስ ለእንደዚህ ዓይነት የከተማ አመጽ ተዳረገ የሚል ነገር ያብራራ አካል የለም፡፡ ይህ ፍረጃም ለብዙ ሰዎች ነገር መወራወሪያ ሰበብ ሆኗል፡፡ፍረጃው ይዘነው መጥተናል ከተባለው የመደመር ፍልስፍና ጋር እንዴት እንደሚገጣጠምም ያብራራ ወገን የለም፡፡

በኦሮሚያና ሶማሌ ኣዋሳኝ ቦታዎች እየተፈጸመ ስላለው ግዲያ፣ ማፈናቀል፣ ውድመት ፣ ወዘተ ያለን መረጃ በነፃ መገናኛብዙሃን አልተረጋገጠም፡፡የድሬዳዋ መገናኛብዙሃን ጋዜጠኞችን መኪናቸውን አስቁሞ ማን እንደገደላቸውና እንዳቆሰላቸው የነገረን የለም፡፡

ሕዝብ ከመንግሥት የሚጠብቀው ግልፀኝነትና ሕግን ማስከበር ነው፡፡ ግልፀኝነት ተጠያቂነትን ያሰፍናል፣ሕግ ማስከበር አቅመቢስን ከጉልበተኛ፣ሰራተኛን ከቀማኛ ያድናል፡፡ ይህ ሁሉ ግን አሁን ያለ አይመስልም፡፡

አሁን ደግሞ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ተገድለው ተገኝተዋል። ይህ ጉዳይ መልዕክቱ ብዙ ነው፡፡ ተገድለው የተጣሉበት ቦታ በራሱ ብዙ ነገር ያስብላል፡፡ ሌላ ቦታ ተገድለው ከመጡ በኋላ መስቀል አደባባይ ጥለዋቸው ሄዱ? ቦታውንስ ለምን መረጡት? ወይስ ኦፕሬሽኑ የተከናወነው እዚሁ ቦታ ላይ ነው? በአካባቢው ያሉ ኤምባሲዎችስ ስለዚህ ጉዳይ የሚያውቁት ነገር የለምን? (መቼም ኤምባሲ ሁሉ ሰላይ እንደሆነ ይታወቃል)፣  ገዳዮቹ እነማንም ይሁኑ እነማን ተገድለው የተጣሉበት ቦታ ግን ግዙፍ ትርጉም አለው፡፡

ጠቅላይሚኒስትራችሁንም፣ የጦራችሁን ኤታማዦር ሹምም፣ሌሎች አይከኖቻችሁን በሙሉ እንዲህ ባደባባይ መረሸን እንችላለን ነው- መልዕክቱ፡፡ መስቀል አደባባይን በሚያህል ግዙፍ ቦታ እንዲህ ዓይነት ዘግናኝ ነገር መፈጸም ሌላ ትርጓሜ ሊኖረው አይችልም፡፡

በደርግ ዘመን ኢሕአፓና መኢሶን የተጨፋጨፉት በዚህ መንገድና ሁኔታ ነበር፡፡አገር የትውልድ ክፍተት ውስጥ ገብታ እስካሁን ድረስ ኪሳራ የምታወራርደውም በዚያ ሐጢዓት ነው፡፡ የከተማ አናርኪዝም፣አደገኛና የዜጎችን ውሎ መግባት አደጋ ውስጥ የሚጥል፣ በመንግሥትና በሕዝብ መሀል አለመተማመንን የሚያነግስ እኩይ ድርጊት መሆኑ በሌሎች ሀገራትም ሆነ በእኛ ሀገር የታየ ሀቅ ነው፡፡Dire tube

 

 

more recommended stories