የኢ.ሶ.ክ ፕሬዝዳንት የአመራርነት ስልጠና ሲከታተሉ የነበሩ የክልሉ መካከለኛ የአመራር አካላት መዝጊያ ሥነ-ስርዓት ላይ መገኘታቸው ተገለፀ

ጅግጅጋ (KaliTimes) ሐምሌ 21/2010ዓ.ም ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ዞኖች፣ ከተማ መስተዳድሮችና ወረዳዎች ለተወጣጡ የክልሉ መካከለኛ አመራር አባላት በክልሉ ሥራ አመራርና ሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ ለተከታታይ 45 ቀናት የሥራ አመራርነት ስልጠና ሲወስዱ ለነበሩ 600 መካከለኛ የሥራ አመራር አባላት በጅግጅጋ ተከማ ቀርያን ዶዳን መሰብሰቢያ አዳራሽ የስልጠናው  መዝግያ ሥነ-ስርዓት እንደተደረገላቸው ተገለፀ።

በመዝግያ መድረክ ዝግጅቱ ላይ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ አብዲ መሀሙድን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ አመራርና ካቢኔ አካላት፣ የክልሉ ም/ርዕሰ መስተዳደሮች፣ ስልጠናውን ያጠናቀቁ የክልሉ መካከለኛ የሥራ አመራሮችና ሌሎች የመንግሥትና የክልሉ መሪ ድርጅት ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች መገኘታቸውም ተገልጿል።

በተጨማሪም በምርቃቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ አብዲ መሀሙድ ኡመር ከተለያዩ የኢ.ሶ.ክ.መ ዞኖች፣ ወረዳዎችና ከተማ መስተዳድሮች ለተወጣጡት 600  መካከለኛ የሥራ አመራር አባላት የሚደረግ የአመራር ስልጠና ምርቃት ሥነ-ስርዓት ላይ በመገኘታቸው  የተሰማቸውን ደስታ ገልፀው፤ በተጨማሪም መካከለኛ የሥራ አመራር አባላቱ በስልጠናው ወቅት ከአሰልጣኞቹ ባሻገር እርስ በርሳቸው በመማማር የተጋሯቸው እውቀትና የልምድ ልውውጦች የበለጠ ሚና ያለው መሆኑን ጠቁመው ስልጠናውን የአመራርነት ሥነ-ምግባርና ስርዓትን በተከተለ መንገድ በመከታተላቸው ለተመራቂዎቹ የላቀ ምስገናቸውን አቅርበዋል።

በሌላ በኩል ክቡር ፕሬዝዳንቱ በስልጠናው ወቅት ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡና የመልካም ሥነ-ምግባር አርአያነትን ላሳዩ የአመራር አባላት ሽልማት ማበርከታቸውም ተገልጿል።

በመጨረሻም መካከለኛ የሥራ አመራር አላባቱ ወደ መጡባቸው ዞኖች፣ ከተማ መስተዳድሮችና ወረዳዎች ሲመለሱ ከሥራ አመራርና ሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ የቀሰሙትን እውቀት፣ ክህሎትና ልምድ ለታችኛው የሥራ ፈጻሚ አካላት እንዲያካፈሉና ህዝብና መንግሥት የጣለባቸውን ሃላፊነትና የዜግነት አደራ በቁርጠኝነትና በአግባቡ እንዲወጡ ክቡር ፕሬዝዳንቱ አሳስበዋል።

more recommended stories